አርባምንጭ ፣ ታህሳስ 25/2017 ዓ.ም
አስተዳደሩ በስማርት ሲቲ ፕሮጀክት ፅንሰ ሀሳብና በአተገባበር ዙሪያ ባለድርሻ ከሆኑ ተቋማትና የዘርፉ ባለሞያዎች ጋር ምክክር አድርጓል።
የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ገዛኸኝ ጋሞ በተገኙበት መድረክ ከተማዋ የቱሪስት መዳረሻ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ከአቻ ከተሞች ጋር ለማቀራረብ አልፎም በተለያዩ ጉዳዮች የሚመጡ እንግዶች እንዲሁም የከተማው ነዋሪዎች ደህንነታቸውን በማስጠበቅና ዘመናዊ አገልግሎት አሰጣጥ ተደራሽ ለማድረግ ከተማ አስተዳደሩ በስማርት ሲቲ ትግበራ ዙሪያ እየተጋ እንደሚገኝ ተገልጿል።
በምክክሩ መድረክ የባለድርሻ ተቋማት ያቋቋሙት የባለሞያዎች ቴክኒክ ቡድን ከአቻ ከተሞች በወሰደው ልምድ መነሻነት የተዘጋጀ የመጀመሪያ ዙር የፕሮጀክቱ ንድፈ ሀሳቦች ቀርበው ግብረመልስ ተሰጥቷል።
በአርባምንጭ ሳታላይት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አማካኝነት የፕሮጀከቱ አካል የሆኑት የመንገድ ዳር መብራት፣ የሕዝብ መዝናኛና መፀዳጃ ማዕከላት፣ መቀመጫ ዲዛይን ለመጀመሪያ ዙር ለትችት ቀርቧል።
መድረኩም የስማርት ሲቲ ትግበራ ወጪ ቆጣቢ፣ የምርት ጥራትና አቅርቦት እንዲሁም የቆይታ ጊዜን ያማከለና በቀላሉ ታዳሽና በመሠረታዊ የከተማ ፕላንና የአርክቴክቸራል ምህንድስና ሳይንስ ስታንዳርዶችን የጠበቀና ጊዜውን የዋጀ ስራ ይጠበቃልም ብሏል።
በውይይቱ የተሳተፉ አመራሮችም የስማርት ሲቲ ዓላማና አስፈላጊነቱ ለከተማው ከሚሰጠው ከፍተኛ ፋይዳ አኳያ በአጭር ጊዜ ተግባራዊ መሆን እንዳለበት አስተያየት ሰጥተዋል።
በመጨረሻም በቀረበው ዲዛይንና የማሻሻያ ሀሳቦች ዙሪያ በአጠረ ጊዜ እርማት በማድረግ ለፕሮጀክቱ ትግበራ ቅድመ ዝግጅቶች እንዲጠናቀቁ አቅጣጫ ተቀምጧል።
ስማርት ሲቲ በከተማው መተግበሩ የዘመኑን ቴክኖሎጂ ደረጃ የሚመጥን ከተማ በመፍጠር የተቋማት አሰራርና መረጃ አያያዝ ዲጂታላይዝ በማድረግ ለህብረተሰቡ ቀልጣፋና ዘመናዊ አገልግሎት እንዲያገኙ እንደሚያግዝ ይጠቀሳል።
በምክክሩ መድረክ የከተማ አስተባባሪ አካላትን ጨምሮ ባለድርሻ ከሆኑ ከአርባምንጭ ሳታላይት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅና ከደቡብ ኢትዮጵያ ዲዛይንና ቁጥጥር ተቋማት አስተባባሪዎችና የዘርፉ ባለሞያዎችና የከተማው ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ተሳትፈዋል።


