አርባምንጭ ፥ ጥር 15/2017 ዓ.ም
ተወዳድሮ ማሸነፍ የሚችል የተሻለ የሰው ኃይልን ከማፍራት አኳያ የቴክኒክና ሳታላይት ኢንስቲትዩቶች ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የአርባ ምንጭ ፓሊ ቴክኒክና ሳታላይት ኢንስቲትዩት ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አባይነህ አበራ ገለፁ ።
የአርባ ምንጭ ፓሊ ቴክኒክና ሳታላይት ኢንስቲትዩት ቦርድ የ2017 በጀት ዓመት 2ኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ላይ ዉይይት አካሂዷል ።
በዉይይቱ በኢንስቲትዩቱ በ2017 ዓ.ም በግማሽ ዓመቱ የተከናወኑ ተግባራት በቦርዱ አባላት በጥንካሬ እና በጉድለት ተገምግሟል ።
ችግር ፈች ለሆኑ ተግባራት ቅድሚያ ተሰጥቶ መሰራት እንደሚገባ በዉይይቱ ተነስቷል ።
ኢንስቲትዩቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚያከናዉናቸዉ አበረታች ተግባራትን በማጠናከር ስልጠናዎችን እስከ ታች ማውረድና የማይነጥፍ የፈጠራ ምንጭ ለመሆን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት እንደሚገባ ተጠቁሟል ።
የኢንስቲትዩቱ ስራ አመራር ቦርድ ከዉይይቱ በተጨማሪ
ተቋሙ ያመረታቸውን ማሽነሪዎችን የጎበኙ ሲሆን በዚህም ከዞን አልፎ ለሀገር ኢኮኖሚ አቅም የሚፈጥሩ ሀብት መሆን እንደሚችልና የገቢ አቅሙን በእጅጉ ማሳደግ የሚችሉ ጊዜና ወጭ ቆጣቢ የፈጠራ ስራዎች መኖራቸውን ተመልክተዋል ።
የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የኢንስቲትዩቱ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አባይነህ አበራ በማጠቃለያው የግንዛቤ ፈጠራና የምዘና ስራዎች እንዲሁም ከለውጥና ከመልካም አስተዳደር ጋር ተያይዞ ያሉ ጉዳዮች ልዩ ትኩረት እንደሚሹ አንስተዋል ።
በተቋሙ የተሰሩ የፈጠራ ስራዎች ከሰርቶ ማሳያነት አልፎ ገበያ ላይ በመቅረብ ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡና ለተቋሙ የሀብት ምንጭ እንዲሆኑ የገበያ አማራጮችን መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል ።
ለዚህም ቅንጅት በሚያስፈልጉ ጉዳዮች ባለድርሻ አካላት በጋራ መስራት እንዳለባቸውና የተቋሙን ከፍታ ለማስጠበቅ መረባረብ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል ።



